ሚታኒ
ሚታኒ ከ1507 እስከ 1288 ዓክልበ. ግድም በስሜን ሶርያ፣ ስሜን ሜስጶጦምያና ደቡብ አናቶሊያ የቆየ ጥንታዊ መንግሥት ነበረ።
ሚታኒ ደግሞ በኬጥኛ ሑሪ፣ በግብጽኛ መተኒ ወይም ናሐሪን፣ በአካድኛ ሐኒጋልባት ይባል ነበር። ከጎረቤቶቻቸው ከኬጥያውያን፣ ጥንታዊ ግብጽና አሦር ጋራ ይታገሉ ነበር፤ በመጨረሻ በ1307 ዓክልበ. ግድም ለአሦር መንግሥት ወደቆ ተገዥ ሆነ።
የያምኻድና የባቢሎን መንግሥታት በ1508-7 ዓክልበ. ለኬጥያውያን መንግሥት ንጉሥ 1 ሙርሲሊ በወደቁበት ጊዜ ያህል በሑራውያን ብሔሮች መካከል የሚታኒ መንግሥት በኪርታ እንደ ተመሠረተ ይታመናል። ሆኖም የግብጽ ፈርዖን 1 ቱትሞስ ከዚያ ትንሽ በፊት (1512 ዓክልበ.) ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶ በ«ናሓሪን» ላይ ዘምቶ ነበርና በአንዱ ጽሑፍ «መታኒ» ሲል ከዚህ ዘመቻ እንደ ሆነ ይታመናል፤ ቀደም-ተከትሉ እንዲህ ከሆነ ምናልባት ኪርታና የሚታኒ ባለሥልጣናት ከሙርሲሊ ዘመቻ በፊት በሑራውያን አገር ወይም ሐኒጋልባት ተመሠረቱ።
«ናሓሪን» የሚለው ግብጽኛ ስያሜ ደግሞ በእብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ አራም-ናሓራይም (አረማይክ ናሓራይን ወይም «ኹለት ወንዞች») ይታያል። እንዲሁም በኪርታ ዘመን ያሕል የአራም-ናሓራይም ወይም እንደ ግሪክኛው የ«መስጴጦምያ» ንጉሥ ኲሰርሰቴም እስራኤልን አሸንፎ ለስምንት አመት እንደ ገዛ ይለናል (መጽሐፈ መሣፍንት 3:8)። «ኲሰርሰቴም» የሚለው ከዕብራይስጥ ስድብ ስለ ተዛበ ትክክል የንጉሥ ስም አይታስብምና የዚህ «ኲሰርሰቴም» መታወቂያ በእርግጡ ገና አልተፈታም።
የሚታኒ ሥርወ መንግሥት አለቆች የሕንዳዊ-ኢራናዊ ቋንቋ ተናጋሪዎች እንደ ነበሩ ይመስላል፤ ከቋንቋቸው የታወቁት ጥቂት ቃላትና ስሞች እንደ ሳንስክሪት፣ የጣኦታቸውም ስሞች ደግሞ እንደ ርግ ቬዳ ጣኦቶች ይመስላሉ። ከዚህ የተነሣ የሚታኒ ባለሥልጣናት በኋላ ሜዶንና ማዳይ ከተባለው አካባቢ (አሁን አዘርባይጃንና ስሜን ፋርስ) የደረሱ መስፍኖች እንደ ነበሩ ይታስባል። የገዙአቸው ተራ ሕዝቦች ቋንቋ ግን ሑርኛ ሲሆን በጊዜ ላይ አለቆቹም ሑርኛ ይናገሩ ነበር።
- ኪርታ 1507-1497 ዓክልበ. ግ.
- 1 ሹታርና 1497-1480 ዓክልበ. ግ.
- ባራታርና / ፓርሻታታር 1480-1457 ዓክልበ. ግ.
- ሻውሽታታር 1457-1417 ዓክልበ. ግ.
- 1 አርታታማ 1417-1407 ዓክልበ. ግ.
- 2 ሹታርና 1407-1393 ዓክልበ. ግ.
- አርታሹማራ 1393-1387 ዓክልበ. ግ.
- ቱሽራታ 1387-1357 ዓክልበ. ግ. (በምዕራብ)
- 2 አርታታማ 1387-1357 ዓክልበ. ግ. (በምሥራቅ)
- 3 ሹታርና 1357 ዓክልበ. ግ.
- ሻቲዋዛ (ኪሊ-ተሹብ) 1357-1327 ዓክልበ. ግ. (የኬጥያውያን ተገዥ)
- 1 ሻቱዋራ 1327-1307 ዓክልበ. ግ. (ለአሦር ወደቀ)
- ዋሳሻታ 1307-1287 ዓክልበ. ግ. (ለአሦር ተገዥ)
- 2 ሻቱዋራ 1287-1277 ዓክልበ. ግ. (ለአሦር ተገዥ)
- ኢሊ-ኢፓዳ 1277-1247 ዓክልበ. ግ. (የአሦር አገረ ገዥ ንጉሥ) ከዚህ በኋላ ሐኒጋልባት ወደ አሦር ግዛት ተጨመረ።